Fana: At a Speed of Life!

ዴንማርክ በአረንጓዴ ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴንማርክ በአረንጓዴ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምታስቀጥል አስታወቀች።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱን ክሮግስትራፕ እንደገለጹት፤ በዳኒሽ አፍሪካ ስትራተጂ አማካኝነት ዴንማርክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን ትብብር ታጠናክራለች።

በግብርና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በማህበራዊ ሴፍቲኔት እና ሌሎች መስኮች ላይ ዴንማርክ በኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታስቀጥል ገልጸው፤ ድጋፉ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

በቀጣይም ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ሌሎች መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን ጠቁመዋል።

በፈረንጆቹ ከ2025 እስከ 2029 ድረስ በዴንማርክ የታቀደው የድጋፍ እቅድ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም እንዲሁም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በዚህም አሁን እያደረገች ካለው ድጋፍ በተጨማሪ በደን ልማት፣ በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ በካርቦን ልቀት ቅነሳ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተግባራት ላይ ሀገራቸው አስተዋጽኦ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

በውሃና ኢነርጂ፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በግብርና መስክ የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት መኖሩንም አምባሳደር ክሮግስትራፕ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አድንቀው፤ መርሐ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ ያስቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የዴንማርክ መንግስት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለዘላቂ የደን ልማት ስራ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በተጨማሪም በአቅም ግንባታ፣ በትምህርት፣ በሪፎርም፣ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ ለማሳደግ በሚሰሩ ስራዎች ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.