Fana: At a Speed of Life!

ጎረቤት ሶማሊያውያን ጦርነት ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ ቀጣናውን ወደ ቀውስ እንዳይከቱ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎረቤት ሶማሊያውያን የራሳቸው ያልሆነ ጦርነት ወደ ሀገራቸው በመጋበዝ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ወደ ቀውስ እንዳይከቱ ሲሉ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች በአፍሪካ ቀንድ እየተስተዋሉ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

የክልሉ የሀገር ሽማግሌ ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሐመድ በውይይቱ ላይ÷ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ሁሉ የሶማሌ ክልል ህዝብ ጉዳት በመሆኑ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን የሀገርን ጥቅም ለማስከበር መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የተለያዩ ሀይሎች ወደ ሶማሊያ መጥተው የአፍሪካ ቀንድን ለማበጣበጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም እንቃወማለን በማለት ገልጸው፤ ሀይሎቹ ለጎረቤት ሶማሊያ ህዝብ ጥቅም የሚያመጡ ሳይሆኑ ጦርነት በመክፈት ችግር የመፍጠር ዓላማ ያላቸው በመሆናቸው ህዝቡ ሊቃወማቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሶማሌ ክልል ህዝብ እና የሶማሊያ ህዝብ ድንበር ቢለያቸውም ወንድማማቾች በመሆናቸው የአብሮነት ታሪካቸውን ሊጠብቁት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማረጋገጥ የምትሰራቸውን ስራዎች የሶማሌ ክልል ህዝብ እንደሚደግፍም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

የባህር በር ጥያቄ አብረን የምናድግበት እንጂ የሚያራርቀን አጀንዳ እንዳልሆነ ለጎረቤቶቻችን ሶማሊያውያን ማሳወቅ እንወዳለን ሲሉም ነው የተናገሩት።

የሶማሊያ መንግስትም ውሳኔውን እየተቃወሙ ያሉ ህዝቦቹን ሊያዳምጥ ይገባዋል ማለታቸውንም የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከ500 ሺህ በላይ የሶማሊያ ስደተኞች በኢትዮጵያ መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ባለፋት ዓመታትም በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞች መጠለያቸው ኢትዮጵያ እንደነበረችና ሀብት ንብረትም ማፍራታቸው ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ እና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እየተማሩ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና የሶማሊያ ህዝብ ሽብርተኝነትን አብሮ እንደተዋጋ፣ ሰላምን የሚያደፈርስ ሌላ ኃይል በመካከል ሊገባና ሊጎዳን አይገባም፤ ይህን ሁሉም ሊረዳው ይገባል ሲሉም የሀገር ሽማግሎዎች ጠቁመዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ኡጋዝ አሊ በበኩላቸው፥ ሶማሊያ ከሩቅ ሀገራት ይልቅ ከጎረቤቶቿ ጋር በመወያየት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ አግባብ ልትፈታ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከውጭ የሚመጡ ኃይሎች የኢትዮጵያንና የሶማሊያን ጉርብትና ከማበላሸት ያለፈ ዓላማ አይኖራቸውም ብለዋል።

ወጣቶችና ሴቶችን ወክለው በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎችም፥ ሶማሊያውያን ችግር በገጠማቸው ጊዜ ሁሉ ቀድማ የምትደርሰው ኢትዮጵያ እንደሆነች ጠቁመው፤ ይህ አጋርነት እንዲቀጥል የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድን በእጅ አዙር ችግር ውስጥ ለማስገባት የሚጥሩ ኃይሎች ዕድል እንዳያገኙ ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.