የኢትዮ-ቻይና ትብብር የሀገራቱን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መምጣቱ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ቻይና ኢንቨስመንት እና የልማት ትብብር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እያሸጋገረ መምጣቱን በቻይና ሳውዝኢስት ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ዋንግ ዢንግፒንግ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በታደሙበት ሰሞነኛው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባኤ፥ ኢትዮጵያና ቻይና 17 የመግባቢያ ሰነዶችን መፈራረማቸው ተገልጿል።
ፕሮፌሰሩ ዋንግ ዢንግፒንግ፤ የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት በግንባታ፣ በኢንዱስትሪና በተለያዩ ኢንቨስመንት ዘርፎች በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲጎለበት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ያነሳሉ።
በኢንዱስትሪዎች በኩል የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድም ኩባንያዎቹ ውጤታማ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዘንድሮው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ጉባዔ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ የአፍሪካ ሀገራትን በልማትና ሌሎች መስክ ለመደገፍ አዲስ ኤኒሼቲቭ ይፋ ማድረጋቸው ትብብሩን ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በተለይም በትምህርት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ቢያጠናክሩ በሰው ኃይል ግንባታ ላይ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ያነሱት።