Fana: At a Speed of Life!

ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሮ ይውላል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን “ሕብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ለሉዓላዊነት ለተከፈለው ዋጋ ክብር በመስጠት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በዕለቱ ከቀኑ 6 ሰዓት ሲሆን ለሁለት ደቂቃ ኢትዮጵያውያን ባሉበት በመቆም ለሉዓላዊነት ለተከፈለው ዋጋ ክብር የመስጠት ስነ-ስርዓት እንደሚያካሂዱ ተገልጿል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የሉዓላዊነት ቀንን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ የጳጉሜን ወር ሲታሰብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀናቱን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች በመሰየም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምንመካከርባቸው፣ ሀገር ለመገንባት የምንጓዝበትን መንገድ የምንፈትሽባቸው እንዲሁም ለሀገር ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ዜጎችን በክብር የምናስብባቸው ቀናት መሆናቸውን እንረዳለን ብለዋል፡፡

ዘንድሮም በጳጉሜን ቀናት ከሚታሰቡ ዓበይት ጉዳዮች መካከል የሉዓላዊነት ቀን አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ቀኑን አስመልክቶ በነገው ዕለት የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ ዋና ዓላማ አያት ቅደመ አያቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት ያላስደፈሩትን የሀገር ነፃነት እና ክብር፣ የእኛ ትውልድም የሚገጥሙትን ፈተናዎች ወደ መልካም ዕድል በመለወጥ ነፃነቷን ጠብቀን ዕድገቷ የተረጋገጠ፣ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስን በተመለከተ መልዕክት ማስተላላፍ ነው ብለዋል፡፡

ጀግኖች ለከፈሉት ዋጋ የምስጋና መልዕክት እንደሚተላለፍና በሳይንስ ሙዚየም ዓውደ ርዕይ እንደሚከፈት፣ ሉዓላዊነትን አስመልክቶ የተዘጋጀ የሕፃናት የህብረት መዝሙርም ይፋ እንደሚደረግና የፓናል ውይይትም እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በሀገር ደረጃ ከቀኑ 6 ሰዓት ሲሆን ለሁለት ደቂቃ ኢትዮጵያውያን ባሉበት በመቆም ለሉዓላዊነት ለተከፈለው ዋጋ ክብር የመስጠት ስነ-ስርዓት ተከናውኖ የዕለቱ ዝግጅት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የሉዓላዊነት ቀኑን ያዘጋጁት የመከላከያ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መሆናቸው ተመላክቷል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.