Fana: At a Speed of Life!

የአማራና አፋር ክልሎችን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራና አፋር ክልሎችን መልካም ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል የሠላም ውይይት በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የሁለቱም ክልሎች በየደረጃው ያሉ አዋሳኝ መዋቅሮች የፀጥታ ተቋማት የሥራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ የአማራ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ደሳለኝ ጣሰው÷ የሁለቱ ክልል ህዝቦችን አንድነት ለማፅናት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የክልሎቹ ነዋሪዎች በመከባበር እና በመቻቻል አንድ ሆነው የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነትን የሚዳፈሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በጋራ በመከላከል ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯ እንድትቀጥል ያደረጉ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ፣ አመራሩና የፀጥታ አካላትም ተናበው መስራት በመቻላቸው የፀረ ሠላም ሃይሎች አላማ እንዲከሽፍ መደረጉን በመግለጽ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የአንድነታቸው ትስስር መቀጠሉንም አንስተዋል፡፡

ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠል ከአመራሮቹ በቀጣይ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።

የአፋር ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ገዶ ሀሞሎ÷ የህገ ወጥነት መስፋፋት ለሠላም መደፍረስ መንስዔ መሆኑን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ህገ-ወጥ የሠዎች ዝውውር ለግጭቶች መስፋፋት አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ በዚህ ዙሪያ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች÷ በሁለቱ ክልሎች የሚኖሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለዘመናት በፍቅር ተሳስበውና ተከባብረውና ተዋልደው አብረው እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለተሻለ ውጤት ለጋራ ስኬት ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባው የገለጹት ደግሞ በሠላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝምና መንግስታት ግንኙነት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኝ ሀይሌ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.