የአዲስ አበባ ፖሊስ የከተማችንን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ሪፎርም እያካሄደ የከተማችንን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን በትጋት እና በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በዛሬው የሪፎርም ቀን 24ኛ ዙር የአዲስ አበባ ፖሊስ መኮንኖችን መርቀን ወደ ስራ አስገብተናል ሲሉ ገልጸዋል።
የሪፎርም አንዱ መሰርት የተጣለው በጸጥታ ሃይላችን ውስጥ መሆኑ ይታወቃል ያሉት ከንቲባዋ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስም ሪፎርም እያካሄደ የከተማችንን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን በትጋት እና በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የዛሬ ተመራቂዎች ስልጠና እና ምርቃትም በሪፎርሙ የጀመርነው ፖሊስን በስነ ልቦና፣ በቴክኒክ፣ በታክቲክ እና በሰው ሃይል የማጠናከር ተግባር አካል መሆኑንም ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የህብረተሰቡን አጋርነት በልኩ የሚጠቀም የፖሊስ ሃይል ሀገር ያሻግራልና በከተማችን የጀመርናቸው ስራዎችን እንዲሁም እቅዶቻችንን እውን ለማድረግ ሀላፊነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ከራሱ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ የህዝቡን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስቀድም፣ የአገልጋይነት ስብዕና የተላበሰ የፀጥታ ሐይል በመሆን ህዝባችሁን ያለአንዳች አድልዎ በታማኝነት እና በቅንነት እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ ብለዋል በመልክታቸው።