የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የአፍሪካ ክትመት ቃልኪዳን ሰነድ በማውጣት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የአፍሪካ ክትመት ቃል ኪዳን ሰነድ በማውጣት ተጠናቋል።
“ዘላቂ ክትመት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ሀሳብ ላለፉት ሶስት ቀናት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ የነበረው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በፎረሙ ማጠቃለያ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ÷ አዲስ አበባ ባዘጋጀችው በዚህ ታሪካዊና ስኬታማ የመጀመሪያ ፎረም የወጣው ቃል ኪዳን ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
የጋራ ሀሳቦች የተንፀባረቁበትና የልምድ ልውውጥ የተደረገበት እና ለአፍሪካ ክትመት ሽግግር ወሳኝ ፋይዳ የሚጫወት መድረክ እንደነበር ገልፀዋል።
ከተሞችን ማዘመንና ዘላቂ ዕድገት ያላቸው ማድረግ ይግባል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የበለፀጉ ከተሞችን በመገንባት ሁሉንም አፍሪካዊ ተጠቃሚ ማድረግ የትብብር ስራ ይጠይቃል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው የአዲስ አበባ የክትመት ቃል ኪዳን ዘላቂና የዕድገት ሽግግር መሰረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከተሞች ዘላቂ ዕድገት የሚያረጋግጡ እና ችግሮችን የሚቋቋሙ፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ አካታች እንዲሆኑ እንዲሁም ያላቸውን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።
ክትመት የሚያመጣቸውን ፈተናዎች እንደ ዕድል በመጠቀም ለተሻለ አህጉራዊ ልማትና ዕድገት በትብብር መስራት አለብን ብለዋል፡፡
በዚህም የተቀመጡ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግቦችን እና የነገ የጋራ ህልማችንን ዕውን ለማድረግ ያግዛል ማለታቸው ኢዜአ ዘግቧል፡፡