የባህል ህክምናን በጥናት በመደገፍ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህል ህክምናን በጥናትና ምርምር በመደገፍና ከዘመናዊ የህክምና ጋር በማቀናጀት አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአፍሪካ የባህል ህክምና ቀን “ጥራት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህል መድሃኒቶች አቅርቦትን በተገቢው የቁጥጥር ዘዴዎች በመደገፍ ማቅረብ” በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።
የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ረጋሳ ባይሳ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ የባህል መድሃኒት ጥራቱና ደህንነቱ ተረጋግጦ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው።
በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችና የባህል መድሃኒት አዋቂዎች በስልጠናና በልምድ ልውውጥ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የባህል መድሃኒቶችን በጥናትና ምርምር በመደገፍና ከዘመናዊ የህክምና ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በ2016 ዓ.ም ከ1 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑ የባህል መድሃኒቶችን በመመዝገብ ጥራታቸውንና ደህነታችው የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ አብዛኛው ማህበረሰብ የባህል ህክምና ተጠቃሚ እንደሆነ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት የባህል መድሃኒት የማዘጋጀት ስራ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እውቅና ለመስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን አንስተዋል።