የለውጡ መንግስት ለሕዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል – አፈ-ጉባዔ አገኘሁ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የለውጡ መንግስት የሕዝቦችን እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አድርጓል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
አፈ-ጉባዔው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ባለፉት ጊዜያት እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ያነሱ አካላት በርካታ ሰብዓዊ ቀውስ ይደርስባቸው ነበር ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግስት ካስተላለፋቸው ታሪካዊ ውሳኔዎች መካከል በቀድሞው ደቡብ ክልል ይኖሩ ለነበሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ እንዲመሰረት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ በሰላምና ጸጥታ፣ በግብርና እና በሌሎች አያሌ የልማት መስኮች እየታየ ያለው የላቀ ውጤት የሕዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ የጀመረውን የውጤታማነት ጉዞ ቀጣይነት ማረጋገጥ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡