Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ ዓመት ለተሻለ ውጤት የምንተጋበት መሆን አለበት – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት ለተሻለ ውጤት የምንተጋበት መሆን አለበት ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን “የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሐሳብ በቦንጋ ከተማ እየተከበረ ነው።

ርዕሰ መሥተዳደሩ በዚሁ ወቅት የጳጉሜን ቀናት አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት በተስፋ የምንቀበልበት ነው ብለዋል።

በእነዚህ አምስቱ ቀናት ባለፈው ዓመት የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የምንተጋበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ቀኑ የመሻገር ጥሪቶች የሆኑት ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ቱሪዝም፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያንና በስንዴ ልማት የተመዘገቡ ውጤቶች የሚዘከሩበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በግብርናው ዘርፍ በተለይም በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም አጠቃላይ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችና የተወሰዱ ርምጃዎች ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።

በቱሪዝም ዘርፍም በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ሀብት በማመንጨት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ክልሉም ከዚህ ተጠቃሚ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.