በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት መሻገርን የሚያመላክቱ ናቸው – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት መሻገርን የሚያመላክቱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒሰረትር መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሻገር ቀንን አስመልክቶ “ከዘመን ወደ ዘመን በተስፋ እንደምንሻገር ሁሉ ከድህነት ወደ ብልጽግና እንሻገራለን” በሚል መሪ ሃሳብ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
አቶ መላኩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት በተለይም ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሥራዎች ጀምሮ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ውጤቶች መሻገርን የሚያመላክቱ ናቸው።
ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ ገቢ ምርትን በመተካት፣ የወጪ ምርትን በማሳደግና የሥራ ዕድልን በማስፋፋት ረገድ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
የሕግ ማዕቀፎች አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ እንዲሆኑ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልና ሌሎች ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በፊት በባንኮች ከሚቀርበው ብድር ውስጥ 70 በመቶው ለመንግስት፣ 30 በመቶው ደግሞ ለግሉ ዘርፍ እንደነበር ጠቁመው÷ በአሁን ወቅት 80 በመቶው ለግሉ ዘርፍ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ለመንግስት ብድር እንዲቀርብ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ59 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለመሳደግ እንደታቀደ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡