Fana: At a Speed of Life!

ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለጳጕሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም፣ የመሻገር ቀን በሰላም አደረሳችሁ! -የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን ጳጉሜን 1 “የመሻገር ቀን” አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለጳጕሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም፣ የመሻገር ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ/ም በዛሬው ዕለት በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች “የመሻገር ቀን” በሚል ስያሜ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፡፡ ዕለቱ “የመሻገር ጥሪቶች፣ የአዲስ ብርሃን ወረቶች በሚል መሪ ቃል” ይከበራል፡፡
መሻገር ከአንዱ ወደ ሌላኛው የሕይወት ምዕራፍ ሽግግር የምናደርግበት ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። አሮጌዉ ዘመን ተጠናቅቆ ወደ ዐዲሱ ዓመት የምንሸጋገርባት የጳጕሜን ወር የመጀመሪያው ዕለትን ስናከበር በተጠናቀቀዉ ዓመት ስኬቶችን ያስመዘገብንባቸው ጠንካራ የለውጥ ሂደቶችንና የተገኙ አመርቂ ድሎችን በላቀ ደረጃ በማጠናከር የገጠሙንን ተግዳሮቶች ደግሞ በአግባቡ በመገምገምና ለመቅረፍ ቁርጠኝነትን በማሳየት ነዉ።
ባሳለፍናቸው ስድስት የለውጥ ዓመታት በርካታና ውስብስብ ፈተናዎች ተጋርጦብናል፡፡ ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል ጦርነት፣ ግጭቶችና ከፍተኛ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን አስተናግደናል፡፡ ሆኖም ግን በተደረገው የሕዝባችን ትብብር፣ በአመራር ቁርጠኝነትና ጥበብ የተጋረጡብንን ፈተናዎች ተቋቁምን መሻገር ችለናል።
በተለይም ጽንፈኞችና የታጠቁ አሸባሪ ቡድኖች በጠባብ የቡደን ፍላጎት እና ስሜት ተነሳስተው በሀገራችን ሉዓላዊነት ላይ ፈተናና ስጋት ለመደቀን ሞክረዋል። ነገር ግን መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በመውሰድ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባራትን በመከወን የሀገር ህልውናና የግዛት አንድነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
እየተገባደደ ባለው በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን ሊያሻግሩ የሚችሉ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጅቶችን በብቃት በመምራት በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ተሰርቷል፡፡ በተለይም ‘መቼም ቢሆን አይጠናቀቅም’ ተብሎ የቆየው የጋራ አሻራችንና የአንድነታችን ተምሳሌት የሆነው ታላቁ ሕዳሴ ግድባችን በማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሶ ሃይል ወደ ማመንጨት ተሸጋግሯል፡፡
በከፍተኛ ትጋትና ጥራት የለሙ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እምቅ ሃብት ያላት ብቻ ሳትሆን ማልማት የምትችል እና በጎብኝዎች የምትመረጥ ሀገር ወደ መሆን ተሸጋግራለች፡፡
በተለያዩ ምክናቶች ተቀዛቅዘው የነበሩ የአምራች እንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ተሸጋግሯል፡፡ በግብርና ዘርፍ በተመዘገቡት ስኬቶች ታሪክን የቀየረው የስንዴ ምርት ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት የስንዴ ልመና እና ሸማችነት በስንዴ ራስን ወደ መቻል አሸጋግሯታል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተጀመሩ እና እየተገባደደ ባለው ዓመት በተጠናቀቁ ሥራዎችና በተወሰዱ ታሪክ ቀያሪ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ከነበረችበት አዙሪት መሻገር ጀምራለች፡፡
በመሆኑ ጳጉሜን 1’ን ስናከብር ኢትዮጵያን ለማሻገር የተሳኩ ስኬቶችን በማስገንዘብ፣ ቀሪ እዳዎችን የምንሻገርበት አቅጣጫን የሚጠቁሙ ሃሳቦች ላይ በመግባባት ይሆናል፡፡ መጪው ዐዲስ ዓመት ድሎቻችንን ይበልጥ የምናሰፋበትና ተግዳሮቶቻችንን የምንቀንስበት ዓመት በማድረግ በላቀ መነሣሣት መቀበል ይጠበቅብናል።
ቀኑን ስናከብር ዋነኛ ትኩረታችን ከግጭት ይልቅ ሰላምን፣ ከከፋፋይ ትሪክት ይልቅ ለወል ትርክት ቅድሚያ መስጠትን፣ ከመጠላለፍ ይልቅ መደጋገፍን፣ ከቂም በቀል ይልቅ ይቅርታን፣ ከጥላቻ ይልቅ፣ ፍቅርን በማስቀደም ሽግግራችንን በፀና ዐለት ላይ መመሥረት ከሁላችንም ይጠበቃል።
በሽግግር ሂደት ውስጥ ስኬትም ፈተናም እንዳለ ተገንዝቦ ለሚገጥሙ ፈተናዎች ሳንንበረከክ የጀመርነዉን ሽግግር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሳደግ የጋራ ትብብራችን ወሳኝ ነው። ስለዚህም መጪዉ ዐዲስ ዓመት ከእጥረቶቻችን በመማር ስኬቶቻችንን ደግሞ በማጎልበት ኢትዮጵ የአፍርካ የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይዋን እንድታሳካ “የመሻገር ጥሪቶች፤ የዐዲስ ብርሃን ወረቶች” ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ እንመኛለን።
መልካም የመሻገር ቀን!!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.