Fana: At a Speed of Life!

ዓለምን ያጨናነቀው የፕላስቲክ ተረፈ ምርት …

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም የአየር ንብረት መበከል ትልቅ ፈተናዋ ስለመሆኑ በየዕለቱ በየመገናኛ ብዙሃኑ የሚደመጡ የአደጋ ዜናዎች ማሳያ ናቸው፡፡

የአየር ብክለት የሚከሰተው ጎጂ ጋዞች እና ኬሚካሎች ወደ አየር ሲለቀቁ ሲሆን፥ ለዓለም የአየር ንብረት መበከል የተለያዩ ምክያቶች ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡

ስልጣኔ ከተፈጥሮ ጋር መቃረን መስሎ እስኪወሰድ ድረስ የሰጠችንን ከራሳችን በመንጠቅ የቆምንበት ምድር እየከዳችን ጎርፍ፣ መሬት መንሸራተት፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ ሰደድ እሳት፣ ድርቅና ሌሎች አደጋዎችን በየዕለቱ እናስተናግዳለን፡፡

ኢንዱስትሪዎችና ተሸከርካሪዎች የሚለቁት ከፍተኛ ጭስ፣ የደን መጨፍጨፍና በበቂ መጠን ዛፍ አለመትከል እንዲሁም የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ለከባቢ መበከል ዋነኛ መንስዔዎች ናቸው።

እንደ ካርቦን፣ ሃይድሮጂን፣ ኦክሲጅን፣ ናይትሮጅን፣ ሰልፈር እና ክሎሪን ካሉ ንጥረ ነገሮች የሚመረተው ፕላስቲክ፥ በቀላሉ የማይበሰብስ በመሆኑ ለማስወገድ ያስቸግራል።

ፕላስቲክ በአግባቡ እንዲወገድ ካልተደረገ ደግሞ ምድር ላይ ወይንም በውሃ አካላት ላይ ሳይበሰብስ እስከ 1 ሺህ ዓመታት ሊቆይ ስለሚችል አወጋገዱ ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግ በተለያዩ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ያስገነዝባሉ።

የሊድስ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ጥናት መሰረት ዓለም በዓመት 57 ሚሊየን ቶን ፕላስቲክ እንደምታመነጭ ማረጋገጡን ጠቅሶ፤ ፕላስቲክ ለአየር ንብረት መበከል መንስዔ መሆኑን አንስቶታል፡፡

ፕላስቲኮች በውሃ አካላትና በየብስ ብቻ የሚገደቡ ሳይሆኑ ወደሰው ልጅ አካልም እንደሚገቡ የገለጸው የዩኒቨርሲቲው ጥናት ተመራማሪዎች፤ አርቲቪሻል ኢንተለጀንስን በዓለም ዙሪያ ባሉ 50 ሺህ ስፍራዎችን በመለየት ለጥናታቸው ይረዳ ዘንድ ተጠቅመዋል።

ጥናቱ ከከባቢ አየር የሚለቀቀውን ፕላስቲክ እንጂ ወደቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚወሰደውን ወይም በአግባቡ የሚቃጠለው ፕላስቲክ ላይ ያተኮረ እንዳልሆነ በማሳየት፤ 15 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብና መንግስታት ቆሻሻን በአግባቡ እንደማይሰበሰቡና እንደማያስወግዱም ተጠቁሟል፡፡

ሆኖም ጥናቱ ከፍተኛ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች ግሎባል ደቡብ ወይንም አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን እንዲሁም እስያ (ከእስራዔል፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ውጭ) እና ኦሽኒያ (ከአውስትራሊያና ኒውዚላንድ ውጭ) ሀገራት የዓለምን ከሁለት ሦስተኛ በላይ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ያመነጫሉ ብሏል፡፡

የደቡቡ ዓለም ከሰሜኑ አንጻር ዝቅተኛ ገቢ ያለው፣ ከፍተኛ የድህነት ደረጃ የተንሰራፋበት፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ዕድገት ያለበት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የትምህርት እድሎች ውስንነት እና የጤና ስርዓቱ ዝቅተኛ ነው፡፡

በመሆኑም የፕላስቲክ ተረፈ ምርት በእነዚህ ሀገራት የተንሰራፋ ነው የሚለው ግኝት ሳይሆን፥ የፕላስቲክ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የማን ናቸው ካመረቱ በኋላስ መልሶ ለመጠቀም የሚወስዱት እርምጃ ምንድነው የሚለው ሊሰመርበት ይገባል።

ምክንያቱም እንደአብነት አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ድርሻዋ አነስተኛ ሆኖ ሳለ ገፈቱንን ግን ካደጉ ሀገራት በላይ እየተቀበለች እንደምትገኝ ዓለም የሚያውቀው እውነት ነው።

የጥናቱ መሪ ኮስታስ ቬሊስ (ዶ/ር) “ግሎባል ደቡብን ለፕላስቲክ ተረፈ ምርት ብክለት ተወቃሽ ማድረግ የለብንም” ሲሉ ያደጉ ሀገራት ለዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛነት አንስተዋል፡፡

ይህም የጥናቱ መሪ ሃሳብ እውነታውን አለመቀበል ነው የሚል ሃሳብ ያስነሳል፡፡

ምክንያቱም በማደግ ያሉ ሀገራትን የተረፈ ምርቶቻቸው መጣያ በማድረግና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በማቆም ለዓየር ንብረት መበከል ገፈት ቀማሽ አድርጋችኋቸዋል የሚሉ ወቀሳዎች ሲነሱባቸው ይሰማል፡፡

የጥናቱ መሪ አክለውም፥ ለዜጎች አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት የግሎባል ደቡብ ሀገራት መንግስታት አቅም ማነስ እንደሚታይባቸው ገልጸው፥ የፕላስቲክ የተረፈ ምርት አሰባሰብ ላይ ወሳኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የግሎባል ደቡብ ሀገራት በምድራቸው የቆሙት ኢንዱስትሪዎች የሚያመነጩት ፕላስቲክ ተመልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስገዳጅ ማድረግና ወደታዳሽ ሃይል ፊታቸውን ማዞር በብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመከራሉ፡፡

በእነዚህ ሀገራት ላይ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ያቆሙ ሀገራትም መውሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባል፤ በዚህም የዓለም ሀገራት በጉዳዩ ላይ ግልጽ አቋም ሊወስዱና ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፕላስቲኮች ምርት በዓመት ከ440 ሚሊየን ቶን ወደ 1 ሺህ 200 ሚሊየን ቶን በላይ ሊያድግ እንደሚችል ጠቅሶ፥ ምድር በፕላስቲክ መጨናነቋን አንስቷል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.