Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ቻይና የትብብር ግንኙነት ሰፊና ጠንካራ መሰረት ያለው ነው – አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት የትብብር ግንኙነት ሰፊና ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ታዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተሳተፉበትንና በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ የሚገኘውን የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ከፎረሙ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው የትብብር መስኮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በወንድማማችነትና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የትብብር ግንኙነት እንዲኖር የሁልጊዜም ፍላጎቷ እንደሆነ መገለጹን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎች መስኮች ከቻይና ጋር የምትሰራበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን ጠቁመው÷ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ሰፊ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መሪዎቹ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በተፈጥሮ ሃብት ልማት በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን አመልክተዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.