ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን ተከብሮ ይውላል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ጳጉሜን 1 የመሻገር ቀን በሚል ተከብሮ እንደሚውል ተገለፀ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ቀኑን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ “የመሻገር ቀን” ተብሎ የተሰየመው ጳጉሜን 1 ቀን ኢትዮጵያን ለማሻገር በተደረጉ ጥረቶች፣ የተገኙ ስኬቶችንና በሂደቱ የገጠሙ ተግዳሮቶች የሚታሰቡበት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማሻገር ትልቅ አቅም የፈጠሩ ስኬቶች በሁሉም ዘርፎች ቢመዘገቡም የግብርና፣ የኢዱስትሪ፣ የቱሪዝም ዘርፎችና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተመዘገቡት ድሎች ለመሻገር ቀን “የመሻገር ምልክቶች” ሆነው መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ለዘመናት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት መቻሉ ከፈጠርናቸው የመሻገር ጥሪቶች አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተገበርናቸው ዕቅዶችና ኢኒሼቲቮች አማካኝነት በስንዴ ሰብል ዓመታዊ ምርታችን ከነበረበት 50 ሚሊየን ወደ 230 ሚሊየን ኩንታል ማምረት አቅም ተሸጋግረናል ሲሉ ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፉም በተለይን ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በተከናወኑ ተግባራት 2 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ ተኪ ምርቶችን ማምረት መቻሉንና በርካታ አምራች ፋብሪካዎችም ዳግም ወደ ስራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡
3ኛው የመሻገር ቀን ምልክት የተደረገው የቱሪዝም ዘርፉ መሆኑን የጠቆሙት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ በዓመቱ ዘርፉን ወደ እውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች መቀየር የተቻለበት ነው ብለዋል።
ተደብቀው የነበሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ወደ ኢኮኖሚያ ጥቅሞች ለመቀየር በገበታ ለሀገር ከተደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ነባር መዳረሻዎች የማደስና ደረጃቸውን የማሳደግ ጥረት ሌላ የመሻገር ምልክት የሆኑ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል።
4ኛው የመሻገር ማሳያ የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ ውጤት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲሆን÷ በዓመቱ የተሳካ የውሃ ሙሌት ብሎም 2 ተጨማሪ ተርባይኖች ሃይል እንዲያመነጩ ማድረግ የተቻለበት ነው ብለዋል።
በማሳየነት የቀረቡት ዘርፎች በሕዝብ ድጋፍ የተገኙ እንደመሆናቸው ምስጋና የሚቀርብበት ቀን መሆኑንም ሚኒስትሯ አመላክተዋል።
በመራኦል ከድር