Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ  ለአፍሪካ ሀገራት የ51 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዥንፒንግ ለአፍሪካ ሀገራት የስራ እድል ፈጠራ የሚውል የ51 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች  የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የቻይና አፍሪካ ጉባኤ በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ሺ በጉባኤው መክፈቻ  ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ቻይና በአፍሪካ ከ1 ሚሊየን በላይ የስራ እድሎችን መፍጠር የሚያስችል 51 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

ቻይና በአፍሪካ ሀገራት በኢንዱስትሪ፣ ግብርና እና ንግድ እድገት ላይ በርካታ ስራዎችን ስታከናውን መቆየቷን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ይህም ቤጂንግን ለደቡብ ሀገራት ተመራጭ የልማት አጋር አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት 20 አመታት ቻይና እና  አፍሪካ ጠንካራ ግንኙነት መመስረታቸውን አስታውሰው ይህ ግንኑነት ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚገባው አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡

ቻይና ለአፍሪካ የአጀንዳ 2063 መሳካት ድጋፏን  እንደምትቀጥል እና የድህነት ቅነሳና የስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ የአፍሪካን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይም  በትኩረት እንደምትሰራ አስገንዝበዋል፡፡

ቻይና በመጪዎቹ ሶስት አመታት  ከአፍሪካ ጋር በዕውቀት ሽግግር፣ ንግድ፣ የኢንዱስሪ ሽግግር፣ የመሰረተ ልማት ትስስር፣ ስፖርት፣ በጤና፣ግብርናና በእንስሳት እርባታ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣አረንጓዴ ልማት፣ የጋራ ሰላምና ደህንነት ዘርፎቹ በጋራ ለመስራት ማቀዷን አመላክተዋል፡፡

ከ33 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.