ዓለምን እየፈተኑ ያሉ የፀጥታ ችግሮችና ኢ-ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የጋራ መፍትሄ ይፈልጋሉ – አንቶኒዮ ጉተሬዝ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለምን እየፈተኑ ያሉ የፀጥታና ደህንነት ችግሮች እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የሀገራትን የጋራ መፍትሄ የሚፈልጉ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ፡፡
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የዩክሬን፣ የጋዛና ሱዳን ግጭቶች በዓለም ፖለቲካ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አስረድተዋል።
የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሃዊ አለመሆንና ተቋማት በሚፈለገው ልክ አለመስራታቸው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አብራርተዋል።
የደቡብ ደቡብ ግንኙነት ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑንና የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ለዚህ ምሶሶ እንደሆነ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡
የተባባሰው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነትና የፀጥታ ችግሮች አሁንም ትብብርን የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።
በተመድ ውስጥ በሚገባ ያልተወከሉ የአፍሪካን ጨምሮ በሚገባ ያልተወከሉ ሀገራትን ውክልና ለማረጋገጥ የማሻሻያ ስራዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል።
ቻይናን የመሰሉ ሀገራት ከአፍሪካ ጋር የሚሰሩትን የጋራ ስራ ተመድ እንደሚያበረታታ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃመት በበኩላቸው÷ ቻይናና አፍሪካ ለዘመናት ተመሳሳይ ፈተና ገጥሟቸው እንደቆዩ አስታውሰው፤ አፍሪካና ቻይና ለዓለም ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና በጋራ መስራታቸው የሚፈልጉትን እንዲያገኙ ያግዛቸዋልም ብለዋል።
ቻይና ለአፍሪካ የአጀንዳ 2063 የምታደርገው ድጋፍ ውጤት በማምጣቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
አፍሪካ ዛሬም ያልተጠቀመችበትን እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
በአፈወርቅ እያዩ