ጉዞ ወደሀገር ቤት የክረምት ፌስቲቫል ጳጉሜን 3 በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይጀመራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ”ጉዞ ወደሀገር ቤት” የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2016 ድረስ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል።
ፌስቲቫሉን አስመልክቶ የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ በሰጡት መግለጫ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች በሶስት ምዕራፍ ወደሀገራቸው ገብተዋል ብለዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ የሚሳተፉባቸው የተለያዩ ሁነቶች መዘጋጀታቸውንም ገልፀው÷ ከጳጉሜን 3 ቀን ጀምሮ የሚካሄደው ፌስቲቫል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፌስቲቫሉ የፋሽን ትርዒት፣ የስፖርት ውድድሮች፣ ኤክስፖና ሌሎች ተግባራት መካተታቸውን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።