በአዲስ አበባ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ በዚህ ሳምንት ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ መጽደቁን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ወደ ስራ እንደሚገባ የመዲናዋ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ በሰጠው መግለጫ÷ ደንቡ በከተማዋ ውስጥ የባከነ የህንጻ ስር የተሸከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ የተሸከርካሪ ማቆሚያ አቅርቦትን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጿል።
ደንቡ የመንገድ ዳር የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችና የህንፃ ላይ፣ የህንፃ ስር፣ የመሬትስር፣ የመሬት ላይ እና ሌሎች ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ሥፍራዎች ላይ እንደሚተገበር ተጠቁሟል።
ማንኛውም የግል ተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጥ አካል አገልግሎት መስጠት የሚችለው የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራው ብቁ ስለመሆኑ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት ሲችል ብቻ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
ማንኛውም ማህበር ወይም ድርጅት ከባለስልጣኑ ጋር የአገልግሎት ውል ሳይፈጽም ወይም የፈጸመው ውል ሳይታደስ፣ ማህበራት ወይም የግል የተሽከርካሪ ማቆሚያ ድርጅት ያለ ደረሰኝ ወይም በህግ እውቅና ያልተሰጠው ደረሰኝ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን አስገንዝቧል።
የማህበር አባልነትን የሚገልፅ ባለሥልጣኑ ከሚያቀርበው የደንብ ልብስ ውጪ ለብሰው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት መስጠት፣ ውል ከገባው ማህበር አባል ውጪ ለ3ኛ አካል ማስተላለፍና ቀጥሮ ማሰራት፣ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የተረከበውን/ያዘጋጀውን ስፍራ እና መሳሪያዎች ከዓላማው ውጪ ሌላ ተግባር ላይ ማዋል እንደማይቻል አስገንዝቧል።
ያለአግባብ ገቢ ለማግኘት ሲባል የክፍያ ማሽን ማበላሸት የተከለከለ መሆኑንም ገልጿል።
ለተገልጋዮች የተሽከርካሪ ሰሌዳ ሳይለጥፉ አገልግሎት መጠየቅ፣ ባለስልጣኑ በልዩ ሁኔታ ለዲፕሎማቲክ ወይም ለአካል ጉዳተኞች በለያቸው ቦታዎች ላይ መጠቀም እና ለተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ አለመፈጸም መከልከሉን አብራርቷል።
የተከለከሉ ድጊቶችን የፈጸመ የተሸከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ሰጪ አካል እንደጥፋቱ መጠን በወንጀል መጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ በባለስልጣኑ በኩል ከ3 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ እንደሚቀጣ ተመላክቷል፡፡
በመሳፍንት እያዩ