የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ በአካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በክረምት የታቀዱ የአደጋ ስጋት አመራር ሥራዎችን ጨምሮ በዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሐይቅ ሙላት ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት እና በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም በሚቻልበት አሁኔታ ላይ ምክር ቤቱ መክሯል፡፡
በዚህም በዳሰነች ወረዳ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወንን ጨምሮ ከውኃ ሙላቱ በኋላ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የአደጋውን የጉዳት መጠን ለመቀነስም የኮሚቴ አባላት እንዲረባረቡ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን የርዕሰ መሥተዳድር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በጎፋ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የተሰበሰበው ድጋፍ ለቤት ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
የ2017 የትምህርት ዝግጅት፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት፣ የኑሮ ውድነት ማረጋጋት ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የፀጥታ ስራ በተያዘው ዓመት በትኩረት እንዲከናወኑ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
እንዲሁም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናት ድጋፍ አሰጣጥ ደንብ፣ የከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደንብ፣ የዐቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ እና የታራሚዎች ቀለብ በተመለከተ በተዘጋጀ የጥናት ሐሳብ ላይ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በቀረቡ ረቂቅ አዋጆችና ደንቦች ላይ የመከረው ምክር ቤቱ በየዘርፉ የሚሰሩ ስራዎችን በሕግ ማዕቀፍ በመምራትና በአሰራር በመደገፍ ለተሻለ ውጤት ማብቃት የሚያስችሉ መሆኑን በማመን ደንቦችን ከነማሻሻያቸው አፅድቋል።