የከተሞች እድገትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ዩኤን-ኢሲኤ) በአፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ዘላቂ የከተሞች እድገት ላይ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የዩኤን-ኢሲኤ ኮሚሽነር ክላቬር ጋቴቴ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ፎረሙ ቀጣይነት ላለው የአፍሪካ ከተሞች እድገት መሰረት ለመጣል የሚያስችል አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለከተሞች ልማት የሚመደበው በጀት አናሳ መሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ የሚመጡ ተጽዕኖዎችና ሌሎችም ተጓዳኝ ተግዳሮቶች የአፍሪካ ከተሞች በሚጠበቀው ልክ እንዳያድጉ አድርጓል ነው ያሉት።
በከተሞች የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፈረንጆቹ በ2050 በአፍሪካ 60 በመቶ የሚሆኑት ዜጎች የከተማ ነዋሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ዩኤን-ኢሲኤ በአፍሪካ የከተሞች እድገት እንዲፋጠን የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።