Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲሱን የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ አንደሚያደርግ አስታውቋል።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ (ኢ/ር) በሰጡት መግለጫ ÷ በ2016 በጀት ዓመት ተቋሙ 42 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ለ427 ሺህ አዳዲስ ደንበኞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡

በተቋሙ ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በተከናወነ ሥራ 1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ሥራ ማሰናበት የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው÷ከ50 ኪሎ ዋት እስከ 200 ኪሎ ዋት ድረስ የሚጠቀሙ ደንበኞች ድጎማ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መሰረትም 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች የማሻሻያ ታሪፉን 75 በመቶ፣ ከ50 እስከ 100 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች 40 በመቶ እንዲሁም ከ100 እስከ 200 ኪሎ ዋት ደግሞ 4 በመቶ ድጎማ እንደሚደርግላቸው አመልክተዋል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.