በአማራ ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ 4 ቢሊየን ብር የሚገመቱ ተግባራት ተከናወኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን 4 ቢሊየን ብር የሚገመቱ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ጋሻው ተቀባ እንዳሉት÷የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ውጤት እያሰገኘ ነው፡፡
በክረምቱ ከ6 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ8 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በጎ ፈቃደኞች በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ አራት ቢሊየን ብር የሚገመቱ ተግባራት መከናወናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ከተከናወኑት ተግባራት መካከልም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ አቅመ ደካሞችን መደገፍ፣ የሰብል ልማት፣ የጤናና የሰላም ማስፈን ተግባራት እንደሚገኙበት ለኢዜአ ተናግረዋል።