የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ:-
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ በሆኑ ውጫዊ እና ውስጣዊ ችግሮች እየተፈተነች ትገኛለች፡፡ የተጀመረው የለውጥ ጉዞም በመሠረታዊነት ይህንን ነባራዊ ሁኔታ የሚቀይር ነው። ሀገራችንም ሆነ ክልላችን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል እየተዳረገ የሚገኘው በሰላም እጦት ችግር ነው፡፡
በሰለጠነ ዘመን ሀሳብንና ፍላጎትን በውይይትና በምክክር መፍታት እየተቻለ የኀይል አማራጭን እንደ መፍትሔ የወሰደው ታጣቂ ቡድን ሀገረ መንግሥትን በኀይል ከመናድ ጀምሮ አድማሱን እያሰፋ ንፁሃንን ዒላም በማድረግ ከማገትና የሀብት ማጋበሻ መንገድ አድርጎ ከመጠቀም ባለፈ የለጋ ህፃናትን፣ ህይወት ጭምር እየቀጠፈ ይገኛል፡፡
ታጣቂው ኀይል የሚፈፀመው ዝርፊያ፣ እገታና ግድያ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ምልክቶች የሚታዩ ቢሆንም በተለይም ጎንደር ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ድርጊት አሳዛኝና ሆን ተብሎ ታቅዶ የሚፈፀም የጠላት አጀንዳ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አብዛኛው የመንግሥት የፀጥታ መዋቅራችን ውድ ህይወቱን እየከፈለ፣ ቤት ንብረቱንና ቤተሰቡን አስይዞ ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ዘላቂ ሰላም ሲል መሰዋዕትነት እየከፈለ ያለ መሆኑን መገንዘ ያስፈልጋል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጥቂት የሥነ ምግባር ብልሽት ያለባቸው አካላት በዚህ ድርጊት ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል።
ይህን መነሻ በማድረግ የመንግሥት አካላት ሆነው ኅላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የችግሩ አባሪና ተባባሪ በመሆን ህዝብን እየበደሉ ያሉትን አካላት ላይ የተጠናከረ ርምጃ መውሰድ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን የዚህ ድርጊት ተባባሪ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ 14 የፀጥታ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራን እንገኛለን።
ከዚህም በተጨማሪ የክልሉ መንግሥት በጎንደር ቀጠና በሚገኙ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ላይ የሚገኙ የሕዝብን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት የተሳናቸው የአቅምም ሆነ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ኀላፊዎች በየደረጃው ከኀላፊነት በማንሳት ተጠያቂ ለማድረግ በትጋት እየሠራ ሲሆን የተጀመረው የኦፕራሽን ስራም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዋነኛነት የዘረፋ፣ የእገታና ግድያ ፕሮጀክቱ የሚመራው ታጣቂው ቡድን መሆኑን የሚያረጋግጡ መረጃና ማስረጃዎች በመኖራቸው ፀጥታ መዋቅሩ የኦፕሬሽን እቅድ አዘጋጅቶ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን በተከታታይ ጎንደር ከተማ ላይ የታየው አግቶ ገንዘብ ከመቀበል ወደ ገዳይነት የተሸጋገረው የታጣቂ ኀይሉ ድርጊት በፊት ለፊት ግጭትና ጦርነት አልሳካለት ያለውን ሀገር የማፍረስ ግብ የበግ ለምዱን ለብሶ ሕዝቡ ውስጥ ተደብቆ ዘግናኝ ግድያ በመፈፀም ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እንዲነሳና ችግሩ አድጎ ወደ አልተፈለገ አመፅና ግርግር በማሸጋገር ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋረ ተናቦ አገርን የማተራመስ እቅዱን ለማሳካት ያለመ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ጅራፍ እሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንዲሉ ጉዳትና ሃዘን የደረሰባቸው ዜጎቻችን ስብራት ሳያንሰን ሞትንና ጉዳትን ለሌላ የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር በሞቱትና ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖቻችንና ጡት ባላቆሙ ህፃናት ህይወት ላይ እንደ መሳለቅ ይቆጠራል፡፡
ጎንደር ከተማ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ሰሞኑን እየተፈፀመ ያለው ነውረኛ ተግባር እጅግ በጣም ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ድርጊት በመሆኑ የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፡፡ ሆኖም ግን መንግሥትና የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ድርጊቱ እንዲታረምና የሕዝብ እንባ እንዲቆም ለማድረግ የህይወት መሰዋትነት ጭምር እየከፈሉ እየታገሉ ባሉበት ሁኔታ ይህን ዋጋ በሚያሳጣ መንገድ እና እውነቱን በማድበስበስ ችግሩን ለመንግሥት አካል ጠቅልሎ በመስጠት አጥፊውን ሃይል ነፃ ለማድረግ መሞክር አህያውን ትቶ ዳውለውን እንዲሉ የማደናገሪያ አጀንዳ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ሊታረም ይገባል።
ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ሲገባ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ባላቸው ኀይሎች አስተሳሰብ በመጠልፍ ያልተገባ ቅስቀሳና የአመፅ ጥሪ፣ የተሸከርካሪ ገደብ፣ የስራ እንቅስቃሴን ማስተጓጎልና የዜጎችን ህይወት በማጎሳቆል ሕዝቡን ለከፋ የኑሮ ውድነትና ተጨማሪ ቀውስ መዳረግ ውጤት አልባ እና የኋላቀርነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።
በዚህ የተሳሳተ የአጀንዳ ቅስቀሳ እውነቱ እንዲደበቅና የጎንደር ሕዝብ ስቃይ እንዲቀጥል ለማድረግ መሞከር ሚዛናዊውንና አሰተዋዩን የጎንደርን ሕዝብም እንደ መናቅ የሚቆጠር አስነዋሪ ድርጊት በመሆኑ ሕዝባችን ጎንደር ከተማን በሚያዋርድና በሚያወድም ተግባር ላይ እንዳይሳተፍ እና በንቃት እንዲታገለው ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
የክልሉ መንግሥት ከዚህ ጉዳይ ጋር ትስስር ያላቸውን አካላት ተጨማሪ ጥብቅ ማጣራት ካደረገ በኋላ የማያዳግም ርምጃ ወስዶ ለሕዝብ የሚያሳውቅ ሲሆን ሕዝቡ በብሎክ አደረጃጀት ውስጥ ታቅፎ በሰለጠነና በነቃት አካባቢውን እንዲጠብቅ እያሳሰብን በማጣራት ሂደቱ ሕዝቡ በየደረጃው የሚሳተፍበት የሚስጥር ጥቆማ መስጫ ሳጥንና የነፃ የስልክ ጥሪ መስመር በማዘጋጀት ከዚህ ድርጊት ጋር እጃቸው ያለበትን አካላት ተጠያቂ ለማድረግ ሕዝቡ ተባባሪና ተሳታፊ እንዲሆን እየጠየቅን አሁንም የህዝቡን ሰላም በሚያውኩ የታጠቁ ሃይሎች ላይ የማያዳግም ህግ የማስከበር ሥራ እንደሚሰራ ልናረጋግጥ እንወዳለን።
የተፈጠረውን ትክክለኛ ችግር የአውድና የባለቤትነት ቅርፅ በማሳጣት እና መረጃ በማዛበት ከእውነት በተቃራኒ በመቀስቀስና በዚህ ህዝብ ላይ እልቂት ለመደገስ የሚደረገውን የሚዲያ ዘመቻ ህዝባችን ሊነቃበት እና ሊታገለው ይገባል፡፡
መንግሥት ያቀረበውን የሰላምና የድርድር ጥሪ ወደጎን በመተው ከውስጥም ከውጭም ካለ የጠላት ኀይል ጋር በመተባበር አገርን በማፈራረስ ለባዕዳንና ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የሚደረገውን ሩጫ ህዝቡ በትክክል ተረድቶ አሰላለፉን በማስተካከል በስሙ በሚምሉና በሚገዘቱ ነገር ግን ተጨባጭ ድርጊታቸው ክልሉንም ሆነ ኢትዮጵያን የማዋረድ ግብ ያላቸው መሆኑን ተረድተን ከትናንት ታሪካችንም ሆነ ከዛሬና ከነገ ህልውናችን በተቃርኖ የቆሙ ሃይሎችን በመገሰፅም ሆነ በመታገል ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል። ከመቸውም ጊዜ በላይ ለውስጥ ሰላማችን ትኩረት በመስጠት በትብብርና በጋራ እንድንሰራ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም”
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም
ባሕር ዳር