የመድሐኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጤና ተቋማት ላይ የሚታየውን የመድሐኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት 2ኛ ዙር የፓርላማ አባላት እና የክልል ምክር ቤት አባላት ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ ተጠናቋል፡፡
በመድረኩ ከመድሐኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በመንግስት ጤና ተቋማት ላይ የሚታዩ ችግሮችና የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በወቅቱ አለመከፈል በአንዳንድ አከባቢዎች ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ በመሆኑ ሊቀረፍ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ ዝቅተኛ የሆነ የግብር አሰባሰብ ስርዓትና አላስፈላጊ ወጪ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይከፈል ምክንያት ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለክልሉ የሚመደበው በጀት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ የጤና ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷በቅድሚያ መስራት በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥና በጤና ተቋማት ላይ የሚታየውን የመድሐኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በክልሉ የጨመረውን የወባ ስርጭት ለመከላከል ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት እና የመምህራን አቅም መገንባት ላይ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷የትምህርት ቤት ምገባ ስራም በቅንጅት የሚሰሩን ተናግረዋል፡፡
በማቴዎስ ፈለቀ