Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በአኙዋ ዞን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በአኙዋ ዞን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በፒኝውዶ ከተማ የትውውቅና የውይይት መድረክ አካሄዱ።

ውይይቱ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ውይይቱን ርዕሰ መስተዳድሯ አለሚቱ ኡሞድ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) እና በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን መርተውታል።

ርዕሰ መስተዳድሯ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች ህብረተሰቡ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ጋምቤላ በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለች ብትሆንም በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች ተጠቃሚ አልሆነችም ብለዋል።

በመሆኑም ያመለጡንን ወርቃማ ዕድሎች በቁጭትና በላቀ ትጋት የህዝቡን የሠላምና የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ለውጥ ተደርጓል ሲሉ ገልፀዋል።

ባመጣው ውጤት የሚመዘን አገልጋይ አመራር ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር በመወገዱ ህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ተግባራቱን ያለምንም ስጋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ህብረተሰቡ መደገፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አመራሮቹ ከዚህ ቀደም ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በኢታንግ ከተማ፣ ኝግኛንግ ከተማና በሜጢ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.