ሱዋሬዝ ከመጪው ቅዳሜ ጨዋታ በኋላ ከብሔራዊ ቡድኑ ራሱን እንደሚያገል አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዑራጋዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሉዊስ ሱዋሬዝ የፊታችን ቅዳሜ ከሚያደርገው የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በኋላ ለሀገሩ እንደማይጫወት አስታውቋል፡፡
የ37 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች ሀገሩ በመጪው ቅዳሜ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከፓራጓይ ጋር የምታደረገው ጨዋታ የመጨረሻዬ ነው ብሏል፡፡
ለሀገሩ 142 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 69 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ ሲሆን÷ ይህም የዑራጓይ ከፍተኛው ግብ አስቆጣሪ አድርጎታል፡፡
ሱዋሬዝ ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉን አስመልክቶ በሰጠው በእንባ የታጀበ ማብራሪያ÷ “ብዙ አስቤበት የወሰንኩት ውሳኔ ነው፤ ትክክለኛው ጊዜም አሁን ነው” ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ በአሜሪካው ኢንተር ሚያሚ በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ ቀደም ሲል በእንግሊዝ ሊቨርፑል እና በስፔኑ ኃያል ቡድን ባርሴሎና መጫወቱ ይታወሳል፡፡