የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ከነገ ጀምሮ እንደሚያቋርጥ አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው በኤርትራ ውስጥ አገልግሎቱን ለመስጠት ባጋጠመው ከአቅም በላይ በሆነ የአሰራር ችግር ነው፡፡
ስለሆነም ከነገ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ ሲያደርግ የነበረውን በረራ እንደሚያቋርጥ አየር መንገዱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ወደ አስመራ ለመጓዝ ቀድመው ትኬት ለቆረጡ መንገደኞቹ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ በሌሎች አየር መንገዶች የሚጓጓዙበት ሁኔታ እንደሚያመቻች አመልክቷል፡፡
አሊያም እንደአማራጭ በደንበኞቹ ፍላጎት ለትኬት የከፈሉትን ገንዘብ ሙሉውን ተመላሽ እንደሚያደርግ ነው የገለጸው፡፡