5ኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 5ኛው የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ጉባዔ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡
ጉባዔው “ተደራሸነትና ጥራት፡ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት ለሁሉም የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በጉባዔው የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ ተደራሽ፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት በዘላቂነት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለሀገሩ የሚሰራ፣ ብቁ እና በሥነ ምግባር የታነጸ ወጣትና አፍላ ወጣት ለማፍራት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
በሁለተኛው የጤና ሴክተር ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የአፍላ ወጣቶች ጤና ስትራቴጂን ለመተግበር ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ለመጠበቅ ሚኒስቴሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ዘመኑን የዋጀ እውቀትያለው፣ አለምን በሚገባ የሚረዳና በሥነ ምግባር የታነጸ ወጣት በመገንባት ረገድ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል የሥነ-ተዋልዶ ጤናን በትምህርት ቤቶች በግልጽ ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ