Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 2ኛ ሆና ሻምፒዮናውን አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፔሩ ሊማ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ÷ 6 የወርቅ፣ 2 የብር እና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል፡፡

በዚሁ መሠረት አትሌት መዲና ኢሳ በ5 ሺህ ሜትር፣ ሲምቦ ዓለማየሁ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ ጀነራል ብርሃኑ በ800 ሜትር፣ አለሺኝ ባወቀ በ3 ሺህ ሜትር፣ ሳሮን በርሀ በ1 ሺህ 500 ሜትር እና አብዲሳ ፈይሳ በ1 ሺህ 500 ሜትር የተሳተፉበትን ውድድር በበላይነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል፡፡

በተጨማሪም አትሌት መቅደስ ዓለምእሸት እና አብዲሳ ፈይሳ በ5 ሺህ ሜትር የብር እንዲሁም አትሌት ማርታ ዓለማየሁ በ3 ሺህ ሜትርና ኃይሉ አያሌው 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገራቸው ማስገኘት ችለዋል፡፡

ከ134 ሀገራት ተሳትፈው 34 ሀገራት ብቻ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በገቡበት ሻምፒዮና÷ ኢትዮጵያ ከዓለም አሜሪካን በመከተል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለተኛ እንዲሁም ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ6 ወርቅ፣ 5 ብር እና 1 ነሐስ በአጠቃላይ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም 3ኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.