Fana: At a Speed of Life!

አቶ ብናልፍ ከአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ከተቋቋመው የሰላም ካውንስል አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

የሰላም ካውንስሉ ሰብሰቢ አቶ ያየህ ይራድ በለጠ÷ካውንስሉ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በመንግስትና በፋኖ ሃይሎች መካከል ድርድር እንዲደረግ የማቀራረብ ሥራ ለመስራት “ማመቻቸት” ነው ብለዋል።

የሰላም ካውንስሉ በሕዝቡ ነፃ ፈቃድና ፍላጎት የተቋቋመው ግጭቱ ከፍተኛ ተጽዕኖ በህዝቡ ላይ እያሳደረ በመሆኑ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች በዘላቂነት በድርድርና በውይይት ተፈትተው የክልሉ ሰላም ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ካውንስሉ የተቋቋመለት ዓላማ እንዲሳካ ሁለቱም ወገኖች የየድርሻቸውን አዎንታዊ ሚና ሊያበረክቱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ዕገዛ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል።

አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው÷በክልሉ ግጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መንግስት ችግሮች በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

መንግስት ሁለቱንም ወገን አሸናፊ የሚያደርገውና ብቸኛው አማራጭ መፍትሄ በሰለጠነ መንገድ ተወያይቶ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሆነ በጽኑ ስለሚያምን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል።

አሁንም መንግስት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በንግግር ችግሮች እንዲፈቱና ግጭቶች እንዲቆሙ ለማድረግ በሩ ክፍት መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ለመፍታትና የታጠቁ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ በንግግርና በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ መንግሥት ባሳየው ቁርጠኝነት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የነበሩ ግጭቶች መቆማቸውንና ሰላም መፈጠሩን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

የሰላም ሚኒስቴርም ለሰላም ከሚሰራ የትኛውም አካል ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመስራትና ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.