ለአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሠጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅና መርሐ-ግብር ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ ከተሞቻችንን ለወደፊቱ ለዜጎቻችን ክብር የሞላበት የኑሮ ዘይቤን ለማጎናፀፍ የሚመቹ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል።
ከተሜነት እየተስፋፈ የሚሄድ መሆኑ የታወቀ ነው ፥ እኛም ዘላቂ እና ምቹ ከተሞችን ለመፍጠር ሁሉም መሳሪያዎች አሉን ነው ያሉት።
በዚህም የከተማዋን ኮሪደሮች ለማልማት የተረባረቡትን ሁሉ አመስግነው ፥ የዛሬው የእውቅና መርሐ-ግብር የተሻለ የከተማ ከባቢ ለመፍጠር ያሳያችሁትን ትጋት እና ጠንካራ ሥራ የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከመጀመሪያው የሥራ ምዕራፍ ብዙ ትምህርቶች ቀስመናል ፤ አሁን ለሚቀጥለው ምዕራፍ ባላሰለሰ የመሻሻል ሂደት እና የሥራ ሥነምግባር በቀደመው ያሳካነውን ለማላቅ ተነስተናል ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
ዛሬ የአዲሶቹን ኮሪደሮች ልማት በይፋ ስናስጀምር ልማቶቹ እና ጥገናዎቹ ከደረስንበት ምዕራፍ አልፈው የሚሻገሩ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባናልም ብለዋል።
በተጨማሪም ይህን ጠቃሚ ሥራ ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የተሰሩት ኮሪደሮች የሥራ መሪዎች በመላው ሀገሪቱ ተመሳሳይ ሥራ ለጀመሩ 11 ከንቲባዎች ረዳት በመሆን እንደሚያገለግሉም ነው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡