Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ ሰላም በማስፈን ያሉንን የመልማት ዕድሎች ልንጠቀም ይገባል – ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላም በማስፈን ያሉንን የመልማት ዕድሎች ልንጠቀም ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ አሳሰቡ።

በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጡት ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ከኑዌር ዞን ነዋሪዎች ጋር ትውውቅና ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።

በተለይም ልማትና እድገትን ማፋጠን የሚቻለው ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ዘላቂ ሰላም በማስፈን የመልማት ዕድሎች መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሯ ማረጋገጣቸውን ከክልሉ መንስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ያለ ህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸው፤ ለተጀመሩት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች መሳካት በአንድነት መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጋምቤላ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን፥ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ የልማት ስራዎች ሳይከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.