ግብርና ሚኒስቴር በአፋር ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በመቀናጀት በአፋር ክልል ሚሌ ከተማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጡ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ለሁለት አረጋውያን ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ እና የችግኝ ተከላ ስ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።
አቶ አወል አርባ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ግብርና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በሚሌ ከተማ ያስጀመሩት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግንባታው የተጀመረው የሁለት አረጋዊያን መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ለሁለቱም አረጋውያን ቤተሰቦች ቀለብ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ ለ200 ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።