የአየር መንገዱን ገፅታ ሊያበላሽ የሚችል ተግባር በሚፈጽም ማንኛውም ሰራተኛ ላይ እርምጃ ይወሰዳል – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን መልካም ገፅታ ሊያበላሽ የሚችል ተግባር በሚፈጽሙ የማንኛውም ተቋም ሰራተኞች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የስልጠና አካዳሚ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየርመንገድ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን ጉዳዮችና ከጉሙሩክ ኮሚሽን ለተወጣጡ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ አየር መንገዱ ሀገራችንን ከሌላው ዓለም ጋር የሚያስተዋውቅ፤ በመልካም ገፅታ እንድትታይ ያደረገ ከዘመን ዘመን የተሻገረ ተቋም በመሆኑ አንደ ዐይን ብሌናችን የምንጠብቀው ነው ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ለደረሰበት መልካም ደረጃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ኃላፊነታቸውን በተገቢው ሁኔታ መወጣታቸው ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚጣጣም አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸው፤ ሰልጣኞች ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአየር መንገዱን መልካም ገፅታ ሊያበላሹ የሚችሉ ያልተገባ ተግባር በሚፈጽሙ የማንኛውም ተቋም ሰራተኛ ላይ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ሲሉም መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።