አቶ ሽመልስ አብዲሳ 1 ነጥብ 84 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር 1 ነጥብ 84 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈን መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷” የለውጡ መንግስታችን የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ለግብርና ሽግግር የተሰጠው ትኩረት ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
በዚህም ዘርፉ እንዲያሳካ ከተለዩ አራት ዋና ዋና ግቦች መካከል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ስኬትም እንደ ስንዴ እና በቆሎ ያሉ የሰብል ዝርያዎች በኢኒሼቲቭ ታቅፈው በልዩ ሁኔታ እየተሰራባቸው እንደሆነ አመልክተዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመንም በመኸር እርሻ በበቆሎ ኢኒሼቲቭ 1 ነጥብ 78 ሚሊየን ሄክታር መሬት በክላስተር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከእቅድ በላይ 1 ነጥብ 84 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል፡፡
እየተከናወኑ ያሉ የኢኒሼቲቭ ተግባራት ከጥገኝነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር የቤተሰብ ብልፅግናን እዉን ለማድረግ የሚደረገው ጉዞ ተስፋ ሰጪ መሆኑን እያስመሰከሩ እንደሆነም ገልጸዋል።