Fana: At a Speed of Life!

እስራኤል የሃማስን መሪ መግደሏን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ወታደሮች በዌስት ባንክ እያካሄዱ ባሉት ሦስተኛ ቀን ዘመቻ በጄኒን ከተማ የሃማስን መሪ እና ሌሎች ሁለት ታጣቂዎችን መደምሰሳቸው ተገልጿል።

የእስራኤል የፀጥታ ኃይል ባወጣው መግለጫ÷ ዊሳም ካዝም የተባለው የሃማስ መሪ በተሸከርካሪ ውስጥ እያለ በተወሰደበት እርምጃ መደምሰሱንና በአየር በተፈፀመ ጥቃት ደግሞ ሌሎች ሁለት ተዋጊዎች ለመሸሽ ሲሞክሩ ተደምስሰዋል፡፡

በደቡብ ምስራቅ ጄኒን ዛባዴህ ከተማ አቅራቢያ ሌሊቱን ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የፍልስጤም መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ÷ የእስራኤል ወታደሮች በቱልካርም የስደተኞች መጠለያ በህንፃዎችና መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ካደረሱ በኋላ ከተማውን ለቀው መውጣታቸውን ዘግቧል፡፡

የእስራኤል ጦር በትናንትናው ዕለት በቱልካርም የታጣቂ ቡድኑ መሪን ጨምሮ አምስት አባላትን መግደሉን ከማስታወቅ ባለፈ የሰጠው አስተያየት አለመኖሩም ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጦሩ በመጨረሻም “ሽብርን ለማክሸፍ፣ የሽብርተኞችን መሰረተ ልማት ማጋለጥና የታጠቁ አሸባሪዎችን ማጥፋት” ሲል የጠራውን ዓላማ ከፈጸመ በኋላ ጦር ኃይሉን ከአልፋራ የስደተኞች ካምፕ ማስወጣቱን አስታውቋል።

የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደግሞ÷ እስራኤል በዌስት ባንክ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ባካሄደችውና ከዘመቻዎች ሁሉ ትልቁ በተባለለት በዚህ ዘመቻ እስከ አሁን 19 ያህል ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፡፡

በጋዛ ያለው ጦርነት አሁንም እየተፋፋመ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ስጋት እያስከተለ ነው መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.