Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የፀጥታ ተቋማት አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸውን የፀጥታ ተቋማት አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ከተሞች ፎረም “ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሃሳብ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

የፀጥታ ተቋማት የጋራ ውይይት ሲያካሂዱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ እንዳሉት ÷ የፀጥታ ተቋማቱ በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

በፎረሙ ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት ወደ መዲናዋ የሚመጡ የአፍሪካ ሀገራት ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲ አምባሳደሮች፣ በሀገራችን የሚገኙ የትላልቅ ከተማ ከንቲባዎች እና ሚኒስትሮች እንዲሁም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ደኅንነት ማረጋገጥ የፀጥታ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በከተማዋ የተካሄዱ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ፎረሙ በስኬት እንዲካሄድ ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅተው በመስራት እንደወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም መልዕክት መተላለፉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.