የማጅራት ገትር መንስዔዎችና መከላከያ መንገዶች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጎል በልብስ መሳይ ሽፋን የተሸፈነ ሲሆን የአንጎል ሽፋን ብግነት ማጅራትገትር በሚል ይታወቃል፡፡
የማጅራት ገትር ህመም በልዩ ልዩ ህመም አምጪ ተህዋሲያንና ባዕድ ነገሮች የሚፈጠር አደገኛና አጣዳፊ ሲሆን ፥ በተለይ በባክቴሪያ የሚመጣው ማጅራት ገትር በቶሎ ካልታከመ ህይወትን ሊነጥቅ የሚችል ከባድ ህመም መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እንደ ባለሙያዎች ገለፃ ሁሉም ሰው የማጅራ ገትር ተጋላጭ ሲሆን የተጋላጭነት ስፋቱና ክብደቱ ግን ይለያያል፡፡
በማጅራት ገትር በተለየ ሁኔታ የሚጠቁትም ህፃናት፣ አዛውንቶች ፣ የካንሰር ታማሚዎችና የኤች አይቪ/ኤድስ ታማሚዎች፣ የአካል ንቅለ ተከላ ያካሔዱ፣ ኬሞቴራፒ የወሰዱ፣ ለብዙ ጊዜ እስቴሮይድ የሚወስዱ፣ የምግብ እጥረት ያለባቸው፣ በተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል ድክመት ያለባቸውና ክትባቱን ያልወሰዱ እንደሆኑ ይነሳል።
ሆኖም ማጅራት ገትርን ክትባት መውሰድን ጨምሮ በሌሎች መንገዶች መከላከል የሚቻልና በበቂ እና አስተማማኝ ህክምና መፈወስ እንደሚቻል ይገለጻል።
ማጅራት ገትር ጉንፋን፣ የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የቶንሲል ኢንፌክሺን፣ የሳንባ ኢንፌክሺንና የጭንቅላት ቅል ምትን አስታኮ ስለሚከሰት እነዚህን በቶሎ ማከም አልያም እንዳይፈጠሩ በማድረግ ማጅራት ገትርን ማስቀረት ይቻላል።
ማጅራት ገትር በህፃናት ላይ ሲከሰት በአዳጊ አንጎላቸው ላይ መስተጓጎልን በመፍጠር ልጆችን ለስትሮክ፣ ለአንጎል ንዝረት (ኢፒለፕሲ)፣ ለመስማት ችግር ፣ለንቃተ ህሊና መድከም፣ የአስተሳሰብና ትምህርት አቀባበል ችግሮችና ለአይነ ስውርነት የሚዳርግ ህመም መሆኑንም መገንዘብ ይገባል፡፡
በዚህም ህፃናትን በማስከተብ ፤ ቀላል ኢንፌክሽኖችን በመከላከልና በማሳከም ከማጅራት ገትር ልንጠብቃቸው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
የማጅራት ገትር ምልክቶች ምንድናቸው?
ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማንቀጥቀጥ፣ ንቃት መውረድ፣ አንገት ማጠፍ አለመቻል(መገተር)ና እራስ ምታትየማጅራት ገትር ምልክቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ምልክቶች ሁለቱን ካዩ በፍጥነት ሐኪም ማማከር እንደሚገባ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡