የትምህርት ዘመኑን ስኬታማ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 የትምህርት ዘመንን ስኬታማ ለማድረግ ከወትሮው የተለየ የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 26ኛው የትምህርት ጉባኤ እና የትምህርት ንቅናቄ መድረክ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በትምህርት ንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ÷ በክልሉ የተፈጠረውን ሠላም ተከትሎ በ2016 የትምህርት ዘመን በተከናወነው አመርቂ የንቅናቄ ሥራ የተማሪዎችን የቅበላ አፈጻጸም ከ94 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ይህንን አበረታች ሥራ በማስቀጠል በክልሉን በ2017 የትምህርት ዘመን የተቀመጡ ግቦችን ስኬታማ ለማድረግ ከወትሮው የተለየ የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የትምህርት ሥራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት አቶ አሻድሊ ፥ በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ለማሣሳካት አመራሩ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) ÷ በ2017 የትምህርት ዘመን 362 ሺህ 794 አዲስ እና ነባር ቅድመ መደበኛ እና መደበኛ ተማሪዎችን የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።