Fana: At a Speed of Life!

በስልጤ ዞን ለጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን በተደጋጋሚ ለሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ ስጋት ኮሚሽነር ማዕረጉ ማቴዎስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ፥ በስልጢ እና በምስራቅ ስልጢ ወረዳዎች ተከታታይ የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ነው።

በዚህም ክልሉ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል የባለሙያዎች የቴክኒክ ቡድን ያደራጀ ሲሆን ፥ ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ የመለየት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል ።

በተጨማሪም ክልሉና የፌደራል መንግሥት ዞኑንና ማህበረሰቡን በማሳተፍ የዝናብ ወቅት ላይ የሚገኘውን ውሃ ወደ እድል መቀየር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የበጋ ወራት ላይ የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት ጥናቱን መነሻ አድርገው ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በክልሉ ስልጤ ዞን በ2 ወረዳዎችና 8 ቀበሌዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ 6 ሺህ ሰዎች ድጋፍ ቢደረግም በቂ እንዳልሆነም ነው የተገለጸው።

የስልጤ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ወሲላ አሰፋ በበኩላቸው ፥ በበልግና መኽር የለማ 1ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል በውሃ መጥለቅለቁን ገልጸው ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ሰብሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናል ብለዋል ።

በአሁኑ ወቅትም ማሽነሪ አስገብቶ ውሃውን ለማፋሰስ አስቸጋሪ በመሆኑ ዝናቡ ሲቋረጥ ስራው እንደሚከናወን የተናገሩ ሲሆን÷ በጎርፍ አደጋው የተፈናቀሉ ዜጎችን በተለያዩ አካባቢዎች የማስፈር ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል ፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.