Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን እንደማትታገስ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ኢትዮጵያ እንደማትታገስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ማምሻውን በአወጣው መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ከሶማሊያ ሕዝብ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል አሁንም ቁርጠኛ አቋም አላት ብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለዚሁ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡

በሁኔታው ላይ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ ወታደር ያዋጡ አገሮች ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡

የመከላከያ ሠራዊታችንን መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ ተከታታይ መግለጫዎች ሲወጡ ኢትዮጵያ በዝምታ እንድታልፍ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ፍላጐት መኖሩ ይታያል፡፡

ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም፡፡

ይህም በመሆኑ በቀጣናው የብሄራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ህዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያለውን ወቅታዊ አለመግባባት ለመፍታት እንዲያስችል በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይም በንቃት ተሳትፎ አድርጋለች፡፡

በእነዚህ ንግግሮች ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል። የሶማሊያ መንግስት እነዚህን ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡

በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሰላም ተልዕኮ የማዘጋጀት እና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ በቀጣናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ አገራትን ተገቢ የሆኑ ስጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡

ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል፡፡

ቀደም ሲል አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም፡፡

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ከሶማሊያ ህዝብ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል አሁንም ቁርጠኛ አቋም አላት፡፡

ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.