Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የመኸር ወቅት 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት በክላስተር ለምቷል – የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የመኸር ወቅት 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት በክላስተር መልማቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ፥ በ2016/17 የመኸር ወቅት 613 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም 19 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱን እና 17 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታሩ ደግሞ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ዝናብ ዘግይቶ በሚገባባቸውና የበልግን ሰብል አንስተው የሚዘሩ አካባቢዎች ላይ በዘር የመሸፈን ስራ ይቀጥላልም ብለዋል ፡፡

ከተዘራው ሰብል ውስጥም በአብዛኛው የምግብ ሰብሎች የሆኑት በቆሎ፣ ጤፍ ስንዴና መሰል ሰብሎች ሰፊ ድርሻ እንዳላቸውም ነው አቶ ኢሳያስ የተናገሩት፡፡

ቀደም ብሎ የተዘራው ሰብል ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አንስተው፥ ዘግይተው የተዘሩት ደግሞ በቡቃያ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች የማሳ እንክብካቤ ስራ፣ የአረም፣ የ2ኛ ዙር ዩሪያ ማዳበሪያ መጨመር፣ የበሽታና ተባይ ክትትል ማድረግ እንዲሁም ስንዴ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የስንዴ ዋግ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ላይም እንደሀገር ጥሩ የሚባል የኬሚካል አቅርቦት መኖሩን ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል ፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.