Fana: At a Speed of Life!

ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ተከሶ “ዳዊት ድሪባ በዳኔ” በሚል ስም 3 ጊዜ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ወንጀለኛ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቪዬሽን ሕግ ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ የተባለው ተጠርጣሪ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ተከሶ ዳዊት ድሪባ በዳኔ በሚል ስም ሦስት ጊዜ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ደጋጋሚ ወንጀለኛ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

ሰሞኑን በሲቪል አቪዬሽን ሕግ ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ የተባለው ተጠርጣሪ ይገኝበታል፡፡

ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1999 ዓ.ም በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ተከሶ ዳዊት ድሪባ በዳኔ በሚል ስም 3 ጊዜ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ደጋጋሚ ወንጀለኛ መሆኑን ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ታሕሳስ 25 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዘረፋ፣ በቅሚያ፣ በሌብነት፣ በቤት ሰብሮ ስርቆትና በደንብ መተላለፍ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ከፖሊስ የምርመራ ማህደር ማረጋገጥ መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ተጠርጣሪው ኤሊያስ ድሪባ በዳኔ ፣ ጀማል ኑሩ እና ዳዊት ድሪባ በዳኔ የሚሉ ስሞችን በመጠቀም 11 የጦር መሣሪያ መዝረፍ ወንጀል፣ 6 ቅሚያ ወንጀል፣ 3 ሌብነት ወንጀሎች፣ 3 ሰው መግደል ወንጀል፣ 2 ስርቆትና ቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀሎች፣ አንድ ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል፣ ከእስር ማምለጥ ወንጀል እና አንድ ደንብ መተላለፍ የወንጀል ሪከርድ በአጠቃላይ 28 የወንጀል ሪከርዶች ያሉበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ውስጥ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 24 ቀን በዋለው ችሎት ስድስት መዝገቦችን ሦስት ጊዜ አጣምሮ ሦስት ጊዜ በሞት እንዲቀጣ ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑን ከፖሊስ የምርመራ ማህደር መገንዘብ መቻሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

እንደገና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዚያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት በጦር መሣሪያ የታገዘ የዘረፋ፣ ከእስር ቤት የማምለጥና በሌብነት ወንጀል የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ቅጣት ያስተላለፈበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ተጠርጣሪው በውሳኔው መሠረት ማረሚያ ቤት የገባው ይግባኝ ጠይቆ ሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ የተቀየረለት ቢሆንም በድጋሚ ይግባኝ በማለቱ ቅጣቱ ወደ 25 ዓመት ተቀንሶለት ለ17 ዓመታት በማረሚያ ቤት ከቆየ በኋላ በይቅርታ መፈታቱም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.