በአማራ ክልል በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመርዳት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
የማስተባበሪያው ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል ÷ በ21 ወረዳዎች የወንዝ ዳርቻዎችን የመከተር፣ ደለል የማውጣት፣ ባህላዊ መሸጋገሪያዎችንና ሌሎች የመከላከያ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በክረምት በጎርፍ መጥለቅለቅን፣ በመሬት መንሸራተትና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በዚህም 400 ሺህ ሰዎች በክረምቱ ለአደጋ እንደሚጋለጡ በመለየት የዝግጅት መደረጉን ገልፀው በጎንደር፣ ባህር ዳርና ሰሜን ሸዋ ዞን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል 45 ሺህ ኩንታል የአፋጣኝ የመጠባበቂያ የምግብ እህል መያዝ መቻሉን አስታውቀዋል።
ከሰሞኑ በሰሜን ጎንደር ዞንና ሌሎች አካባቢዎች በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተፈናቀሉ 2 ሺህ 949 ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አሁንም በጣና ዙሪያ በሚገኙ የማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ስድስት ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞንና በባህር ዳር ዙሪያ ባሉ የሃይቁ አዋሳኝ አካባቢዎች ስጋት ያለ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።