አቶ ጥላሁን ከበደ በትምህርት ጉዳይ ሁሉም ባለድርሻ ተቀናጅቶ እንዲሰራ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “በትምህርት ጉዳይ መምህራን፣ አመራር እና ወላጆች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል” ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡
‘የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራትና ለሀገር ብልፅግና’ በሚል መሪ ሃሳብ ክልላዊ የትምህርት ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፥ በባለፈው የትምህርት ዘመን ከነበረው ዝቅተኛ መጠነ ማለፍ ለመውጣት ጥረት ተደርጎ መጠነ ማለፍን ማሳደግ ተችሏል።
ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንደተሰጠና አዲስ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ አምና በመጽሐፍ እጥረት የነበረውን ችግር ለመቅረፍም ‘አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ’ በሚል ኢኒሼቲቭ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቶችን ምቹና ሳቢ በማድረግ ልዩ ፍላጎት ያላቸውንና ሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና የትምህርት ስርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ እናደርጋለን ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፥ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የትምህርት ቤት ምገባ አስተዋጽኦ እንዳለው በማመን በ2016 ዓ.ም ከ175 ሺህ በላይ የተማሪዎች ምገባ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በመለሰ ታደለ