አምባሳደር ዮሐንስ አብርሃም የካማላ ሀሪስ የፕሬዚዳንታዊ ሽግግር ቡድን ሀላፊ ሆነው ተመረጡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትውልድ ሀረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዘው አሜሪካዊው አምባሳደር ዮሐንስ አብርሃም የካማላ ሀሪስ የፕሬዚዳንታዊ ሽግግር ቡድን ሀላፊ ሆነው መመረጣቸው ተነገረ።
ዴሞክራቶችን ወክለው በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩትን ካማላ ሀሪስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የመምራት ሃለፊነት የተሰጣቸው አምባሳደር ዮሐንስ የፕሬዚዳንታዊ ሽግግር ቡድን በመምራት ልምድ ያላቸው መሆኑም ገልጸዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ መቀመጫውን ጃካርታ ባደረገው የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሲሆን÷ በቀጣይ ቀናት ስራቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል።
አምባሳደር ዮሐንስ በአዲሱ የስራ ሀላፊነት ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሀሪስ በሚደረገው የምርጫ ሂደት ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ከቻሉ የአዲሷን ፕሬዝዳንት የሽግግር ቡድን በማዋቀር ከመሳተፍም በላይ ፖሊሲ ማርቀቅ ላይም ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ አምባሳደር ዮሐንስ አብርሃም የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የአሜሪካ አምባሳደር ሆኖ በቆዩባቸው ሁለት አመታት የአሜሪካን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
አምባሳደር ዮሐንስ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2020 የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሽግግር ቡድን ዋና ሀላፊ እንደነበሩ ኤንቢሲ ኒውስ በዘገባው አስታውሷል።
ዮሐንስ በባራክ ሁሴን ኦባማ አስተዳደር ዘመንም ለስምንት ዓመታት በኋይት ሃውስ ውስጥ ሙያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።
የ42 ዓመቱ አምባሳደር ዮሐንስ አብርሐም በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቢዝነስ አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍትኛ ማዕረግ ተመርቀዋል።