Fana: At a Speed of Life!

ሀብታችንን በአግባቡ ባለማስተዋወቃችን በወጪ ንግድ ማግኘት ያለብንን ጥቅም እያገኘን አይደለም – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት በአግባቡ ባለማስተዋወቃችን በወጪ ንግድ ዘርፍ ማግኘት ያለብንን ጥቅም እያገኘን አይደለም ሲሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

“የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ከሚገኘው የንግድ ሳምንት ጎን ለጎን የወጪ ንግድን አስመልክቶ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የንግድ ተዋንያን መካከል የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ ሀብታችንን በአግባቡ ባለማስተዋወቃችን በወጪ ንግድ ዘርፍ ማግኘት ያለብንን ጥቅም እያገኘን አይደለም ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድ ከማምረት ይነሳል፤ በወጪ ንግድ ምርቶች ዙሪያ ምን፣ መቼና እንዴት ማምረት እንዳለብን በደንብ ማወቅ እና በመጠን፣ በጥራትና በዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅብናልም ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል የወጪ ንግዱን በማስተካከል ህገ ወጥ የንግድ ስርዓትን በመግታት ረገድ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ ምህዳርን የፈጠረ እንደሆነ አንስተዋል።

ምርትን በብዛትና በጥራት በማምረት ሰፊ የገበያ ትስስርን በመፍጠር የወጪ ንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንደሚገባም ተገልጿል።

በተለይም ደግሞ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት ወደ ሙከራ ትግበራ በቅርቡ እንደሚገባ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በታሪኩ ወልደሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.