Fana: At a Speed of Life!

የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሚናን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለመገናኛ ብዙኃን አመራር እና ባለሞያዎች በሰውሰራሽ አስተውሎት እና የሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የሚዲያ ልምዶችን በመቀየርና አዳዲስ ነገሮችን በማስተዋወቅ ረገድ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ስላለው ሚና አብራርተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው በተቋማቱ ውስጥ የሚዲያዎችን አሰራር ሊያዘምን በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያ እና ዓለማቀፍ ተሞክሮዎችም በገለጻው ተዳሰዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው÷ ቴክኖሎጂው ሌላው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ትልቅ ዕድል ይዞ ስለመምጣቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በየዕለት ተግባራቸው ከመጠቀም ባለፈ ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ሚዲያዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው÷ ቴክኖሎጂው ከይዘት ፈጠራ ጀምሮ እስከ ስርጭት ድረስ ለባለሙያዎች እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

ይህንንም ልምድ በሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሚዲያ ተቋማት ውስጥ ትልቅ ችግር የሆነውን የዳታ ማከማቻ እጥረት ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ እና መገናኛ ብዙኃኑ በቅርበት መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.