Fana: At a Speed of Life!

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ገለጸ።

የፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ እንደገለጹት÷ ማሻሻያው ለዘርፉ እድገት ማነቆ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው የመለዋወጫ ችግር ሳይገጥመው አዳዲስ ማሽኖችን በማስገባት በሙሉ አቅሙ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ በመሰማራት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ኢንዱስተሪ ፓርክ ማሻሻያው ያመጣውን ዕድል በመጠቀም በቅርቡ የወለል ንጣፍ የሚያመርቱ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን አስታወቀዋል።

ይህም እስከሁን ከውጭ ይገባ የነበረውን ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው÷ ሌሎች ጥያቄ ያቀረቡ ባለሃብቶችንም ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል ወደ ፓርኩ የገቡ የጨርቃ ጨርቅና የብቅል ፋብሪካዎች ከውጭ የሚገባውን ምርት ከመተካት ባሻገር የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.